SHARE

በጂግጂጋ ሁከት ተቀስቅሶ ነዋሪዎች ሰላማቸውን ካጡ አምስት ቀናት አልፈዋል። ግጭቱን በመሸሽ በተለያዩ ስፍራዎች ተጠልለው የሚገኙ ዜጎችም ይሁን ከመኖሪያ ቤታቸው የማይወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች የውሃ እና የምግብ እጥረት እንደገጠማቸው ይናገራሉ።

ቅዳሜ ዕለት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ያልሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ለደህንነታቸው በመስጋት በአብያተ-ክርስቲያናትና በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።

ዛሬ (ረቡዕ) በስልክ የነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ የሃገር መከላከያ ወደ ከተማዋ ከገባ በኋላ አንጻራዊ መረጋጋት ቢታይም የምግብ እና የመጠጥ ውሃ እጥረት ግን ለከፋ ችግር እየዳረጋቸው እንደሆነ ነግረውናል።

ለደህንነቱ ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው የከተማዋ ነዋሪ ”ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ተጠልዬ ነው የምገኘው። አሁንም ለደህንነቴ ስለምሰጋ ወደ መኖሪያ ቤቴ መመለስ አልፈልግም። እዚህ ግን ከፍተኛ ችግር እየገጠመን ነው። በዕርዳታ የተሰጠንን ብስኩት ነው እየተመገብን ያለነው። ውሃ ግን አላገኘንም” ብሏል።

ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ ”እስካሁን መንገድ ዝግ ስለሆነ ወደ ከተማዋ የሚገባ ምንም አይነት ነገር የለም። ቤት ውስጥ ያለንን ዱቄት በመጠቀም ቂጣ እየጋገርን ነው እየበላን የምንገኘው፤ እሱም እያለቀብን ነው። ከቀናት በኋላ ምን እንደምንሆን አናውቅም” ስትል ነዋሪዎች የገጠማቸውን የምግብ እጥረት ትናገራለች።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መረዳት እንደቻልነው ከትናንት ማክሰኞ ጀምሮ የቧንቧ ውሃ ተበክሏል የሚል መረጃ በስፋት በመናፈሱ የከተማዋ ነዋሪዎች የመስመር ውሃ ከመጠቀም በመቆጠባቸው የውሃ እጥረቱን ከፍ አድርጎታል።

የክልሉ ተወላጅ የሆነ አንድ ግለለሰብ እንደሚለው ከሆነ ”በመጀመሪያ ደረጃ በጂግጂጋ ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት ነው ያለው። አሁን ደግሞ ውሃው ተመርዟል ተብሎ ሰው በውሃ ጥም እየተሰቃየ ነው” ይላል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ጨምረው እንደነገሩን ከሆነ የጸጥታ አስከባሪዎችም ሆኑ የመንግሥት አካላት ሸሽተው የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ከመጠየቅ ውጪ ምንም አይነት ድጋፍ እየደረጉልን አይደለም በማለት ቅሬታቸውን ነግረውናል።

ነዋሪዎቹ መንግሥተ አስቸኳይ የምግብ እና የመጠጥ ውሃ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል። BBC Amharic

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here