SHARE

ቀዩዋ ፕላኔት ተብላ በምትጠራዉ ማርስ በፈሳሽ ውሀ የተሞላ ሀይቅ ማግኘታቸውን ተመራማሪዎች እንዳስታወቁ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

20 ኪሎ ሜትር ያህል ይሸፍናል የተባለው ሀይቅ በማርስ ደቡባዊ ዋልታ ቀዝቃዛ ክፍል ነው የተገኘው፡፡ ከዚህ ቀደም የተካሄዱ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በማርስ ከርሰ ምድር ለተወሰኑ ወቅቶች ብቻ የሚቆዩ እና የሚፈሱ አነስተኛ የውሀ አካላት መኖራቸወን ይፋ አድርገው ነበር፡፡

ሆኖም ማርስ የሳሳ ከባቢ አየር ስላላት በሚፈጠረው ከፍተኛ ቅዝቃዜ የውሀ አካላቱ በበረዶ ስለሚሸፈኑ ለመለየት አዳጋች ነበር፡፡
ይህኛውን ጥናት ለየት የሚያደርገው በፕላኔቷ ላይ በሁሉም ወቅቶች ሳይነጥፍ የሚቆይ ሀይቅ መኖሩን ማረጋገጥ መቻሉ ነው፡፡

ማርሲስ በተሰኘችው ሳተላይት አማካኝነት የተገኘው ሀይቅ በጣም ሰፊ የሚባል አለመሆኑን እና ጥልቀቱን በትክክል ማስቀመጥ እንዳልተቻለ ሲገመት ከአንድ ሜትር በላይ ሊሆን እንደሚችል ግን የጥናት ቡድኑ መሪ ፕሮፌሰር ሮበርቶ ኦርሴ ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ እንዳሉት በማርስ የተገኘዉ ሀይቅ በምድራችን ዋልታዎች ፣በከርሰ ምድር አለት ውስጥ እና በበረዶ ግግር መካከል እንደሚገኘው ከፊል በረዶ አይደለም፡፡

ይልቁንም በማርስ የተገኘው ሙሉ በሙሉ ፈሳሽ ሀይቅ ነዉ፡፡ ማርስ ህይወት ላላቸው አካላት መኖሪያነት ምቹ አለመሆኗ በጥናቶች ቢታወቅም ፈሳሽ የውሀ አካል መገኘቱ ህይወት ያላቸው ፍጡራንን ለማግኘት የሚደረገውን ጥናት ያግዛል ተብሏል፡፡

ለጊዜው ግን ጥናቱ በማርስ ህይወት ያላቸው አካላት መኖራቸውን የሚያሳይ ፍንጭ አለመገኘቱ ተገልጿል፡፡

የሀይቁን የውሀ ኬሚካላዊ ባህሪ እና የሙቀት መጠን ለመመርመር ከፍተኛ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ገንዘብ ስለሚጠይቅ በዘርፉ ምርምሩን ለመቀጠል ችግር መፍጠሩ ተጠቁሟል፡፡
በቢንያም መስፍን

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here