SHARE

በመደመር ዕሳቤ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ የተለያዩ ስኬቶችን በማስመዝገብ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ለ20 ዓመታት በቁርሾ ውስጥ የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ዳግም ግንኙነታቸውን እንዲያድሱ ከማድረግ በተጨማሪ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በማህበራዊ ዘርፎች አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
ይህም ሆኖ ታዲያ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ጥቂቶች የለውጡን ጉዞ ለማደናቀፍ ሲጥሩ ተስተውሏል፡፡ ድርጊቱ የማያዋጣና የማይበጅ መሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ በማስገንዘብ ከዕኩይ ድርጊቱ ፊትና ጀርባ የቆሙ አካላት የሠላሙን ጎዳና እንዲከተሉ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ እውነታው ይህ ቢሆንም ታዲያ አሁንም በተለያዩ አካባቢዎች የአገሪቱን ሠላምና መረጋጋት የሚያውኩ፣ህዝቡን ለስጋት የሚዳርጉ ግጭቶች እየተከሰቱ ነው፡፡ እነዚህን ዕኩይ ድርጊቶች ለመግታትና የድርጊቱን ተዋናዮች ሥርዓት ለማስያዝ መንግሥት ከሠላም ጥሪው ያለፈ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅቷል፡፡ መንግሥት ሠላምን የማስከበር፣ የዜጎችን በሠላም የመንቀሳቀስ መብትን የማስጠበቅና የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት፡፡
ግጭት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለህግ የማቅረብ፤ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶችን ለመከላከል፣ ለማርገብና ለማምከን የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡና ተጠያቂዎቹንም ለፍርድ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡ በተለይም በሶማሌና ኦሮሚያ ክልል የተከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት የተደረገው ጥረት ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ ባለመቻሉ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ለመግባት ተገዷል፡፡ የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮችም የፌዴራል የጸጥታ ኃይል ጣልቃ በመግባት የጸጥታ፣ የሠላምና መረጋጋት ሥራ እንዲሰራ፤ እንዲሁም የሕግ ማስከበር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ተስማምተዋል። ለአፈጻጸሙም ቅንጅት በመፍጠር አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡
ሠላምን ለማስከበር የተደረሰው ስምምነት እንደ አገር ወሳኝና ተገቢ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ህዝብና አገርን ለስጋት የሚዳርጉና የሚጎዱ ግጭቶችን ማስቆም ጊዜ የማይሰጠውና ህገ መንግስታዊ ግዴታም ነው፡፡ ለሰው ህይወት መጥፋትና አካል መጉደል ፤ ለዜጎች መፈናቀልና ንብረት መውደም ምክንያት የሆነውን ግጭት ማስቆም አስፈላጊ ነው፡፡ የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ፤ ግጭትን የሚያባብሱ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፣ የተፈጠረውን ብሩህ ተስፋ ለማስቀጠል በፍቅርና አብሮነት ሕዝቡ እንዲተጋ፤ ከዚህ በተቃራኒው የሚፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶችን ለመከላከልም ይረዳል፡፡
ይህም ሆኖ ግን በዚህ ድርጊት የተሰለፉ አካላት የሠላሙን ጎዳና በመምረጥ ሂደቱን ለመለወጥና ለማስተካከል ቢተጉ አዋጭና ተመራጭ ነው፡፡ በግጭትና ሁከት የተሰለፋችሁ አካላት የያዛችሁት መንገድ አክሳሪና ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍላችሁ መሆኑን ተገንዝባችሁ ወደ ሠላሙ ጎዳና መቀላቀሉ ይበጃችኋል፡፡ ሠላምን በመጥላት አንዳችም ትርፍ እንደማይገኝ ካለፈው የጥፋት ታሪክ መማር ይቻላል፡፡ በግጭትና ሁከት ያተረፈም፤የተጠቀመም አካል የለም፤ወደ ፊትም አይኖርም፡፡ በግጭት ውስጥ ያለፉና በግጭት ውስጥ ያሉ የጎረቤትና የሩቅ አገራት ተሞክሮም ይህንኑ እውነታ ነው የሚያስረዳን፡፡ ስለሆነም ደማቁን የፍቅርና የይቅርታ ጥሪ በመቀበል በሠላሙ በር መመላለሱ ያዋጣል፡፡ መንግሥት የኃይል እርምጃ ለመውሰድ እስኪገደድ ድረስ ግጭትን በማራገብና በማቀጣጠል የጨለምተኝነት ጎዳና መጓዝ ውጤቱ ትልቅ ዋጋን ከማስከፈል የዘለለ አይሆንም፡፡ በግጭትና ሁከት ድርጊት በቅርበትም ይሁን በርቀት ከመሳተፍ መቆጠብ ይገባል፡፡
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ አክቲቪስቶች፣ጦማርያን አርቲስቶችና በተለያዩ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎችም ግጭትን የሚቀሰቅሱ፣በዜጎች መካከል መቃቃርን የሚፈጥሩ ጽሑፎችና ኪነጥበባዊ ሥራዎችን ከማቅረብ መቆጠብ ይኖርባቸዋል፡፡ የማይበጅ አመለካከትን በህዝብ ውስጥ ከመዝራት ስሜታዊ አባዜ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ህዝብን የሚያጣሉና የሚለያዩ የጥላቻ ጡቦችን ለመደርደር ከመሽቀዳደም ፣ የእርቅና የፍቅር ድልድዮችን ለመገንባት መጣደፍ ይሻላል፡፡
አገር ለልማት ስትተጋ የሁሉም ጥረትና የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ በተለይም የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየተፈታተነ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ የተጀመረውና አበረታች ውጤት እያስገኘ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማሳደግ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ግድ ይላል፡፡ በህገ ወጥ መንገድ የውጭ ምንዛሬ ግብይት የሚያካሂዱና የሚያከማቹ አካላት ከዚህ ድርጊታቸው ሊቆጠቡ ግድ ይላቸዋል፡፡ አገር በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየታመሰች በየጓሮው የውጭ ምንዛሬ ንግድ ማጧጧፍ በአገርና በህዝብ ላይ መቆመር ነው፡፡ ስለሆነም የዚህ ተዋናዮች ህጋዊውን መስመር በመከተል በመንግሥት ለቀረበው ጥሪ ፈጣን ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ኅብረተሰቡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭት ለማስነሳት የሚፈልጉ አካላትን ባለመተባበር ፊት ሊነሳቸውና ለሚመለከተው አካል በመጠቆም ህገ ወጥ ድርጊቱን ለማምከን የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይኖርበታል፡፡ ጊዜው አንድነት የሚሰበክበትና በተባበረ ክንድ ለለውጥና ልማት የሚተጋበት የመደመር ጉዞ እንጂ መከፋፈልና ጥላቻ የሚቀነቀኑበት አይደለም፡፡ ራስን ከህገ ወጥ ድርጊት በማራቅ ለአገር ሠላምና ልማት የሚበጁ ተግባራትን በማከናወን የዜግነት ግዴታን መወጣት ይገባል፡፡ ዘላቂ ሠላምን ለማረጋገጥ፤ኢኮኖሚያ ዕድገትን ለማፋጠን፤ የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከር በሚረዱ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ የሚያፋጁንን ሳይሆን የሚበጁንን፣የሚያለያዩንን ሳይሆን የሚያስተሳስሩንን፣የሚያራርቁንን ሳይሆን የሚያቀራርቡንን ጉዳዮች እያጎላን መጓዙ ነው የሚጠቅመን፡፡ Read More

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here