SHARE

በኢትዮ ፎርብስ ለንባብ ባበቃት መጽሔት ብዙ ሰዎችን ሰላም ሲነሳና በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ላይ ጉልህ ተፅእኖ ሲያሳድር ስለሚስተዋለው መጥፎ የአፍ ጠረን ችግር በእንግሊዝኛ (halitosis or bad breath) የችግሩን ምንነት እና መፍትሔውን አስነብቧል፡፡ ይህ ከጥርስ መቦርቦር እና ከጥርስ አቃፊ ችግሮች በመቀጠል በሦስተኛ ደረጃ የሰውን ልጅ ወደ ጥርስ ሕክምና ክሊኒኮች በማመላለስ የሚታወቀው መጥፎ የአፍ ጠረን ቀላል ችግር ቢመስልም ተገቢው ክትትል ተደርጎ ካልተወገደ ትዳርን እስከማናጋት ሊደርስ እንደሚችል ይነገርለታል፡፡

አንድ ሰው መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳለበት እንዴት ማረጋገጥ ይችላል? አንድ ሰው መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳለበት እና እንደሌለበት በዋናነት በሁለት ቀላል መንገዶች በግሉ ሊያረጋገጥ ይችላል፡፡ ይህም የሚሆነው አንደኛ ንፁህ ማንኪያ ወይም ጠቋሚ ጣታችንን በመጠቀም ወደ ምላሳችን የመጨረሻ ክፍል በመላክ ከላይ ያለውን ነጭ ምራቅ መሰል ዝልግልግ ነገር በመፋቅ እና በማሽተት ለሌሎች ሰዎች ሊሸት የሚችለውን እራሳችን ማወቅ እንችላለን፡፡ በተጨማሪም አፋችንን በመጠኑ በእጃችን መዳፍ በማፈን ትንፋሻችንን ወደ አፍንጫችን እንዲሄድ በማድረግ ያለውን ጠረን አሽትተን ማረጋገጥ እንችላለን። ምንም እንኳ ከላይ እንደተጠቀሰው ዘዴ ሙሉ በሙሉ ትክክለኛውን ሽታ ሊያሳይ ባይችልም፡፡ በሌላ መልኩ መቼም አንድ የልብ ወዳጅ አይጠፋምና መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳለብዎ እና እንደሌለብዎ ወዳጅዎን ጠይቀው ሊረዱም ይችላሉ፡፡ እዚህ ላይ ሳይነሳ መታለፍ የሌለበት ጉዳይ አንድ በዕለት ተዕለት ኑሯችን አብሮን ያለ ሰው መጠፎ የአፍ ጠረን ችግር ቢኖርበት ችግሩን ከመንገር ወደ ኋላ ማለት እንደሌለብን ነው፡፡ ምንም እንኳን በቀጥታ «አፍህ ይሸታል» ብሎ መናገር ቢከብድም ነገሩን አቅልለን ወደ ሕክምና በመሄድ መፍትሔ ሊገኝ እንደሚችል በማመላከት መላ እንዲፈልግ ማድረጉ የተሻለ ውጤት ያመጣል «ለሰው- ሰው ነው ልብሱ» ይል የለ ብሂላችን::

የመጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤው ምንድንነው? መጥፎ የአፍ ጠረንን አስመልክቶ የተፃፉ አብዛኞቹ መረጃዎች መንስኤዎቹን በሁለት ከፍለው ይተነትኑታል፡፡ በቅድሚያ ከአፍ ውስጥ አካላት ጋር በተያያዙ ችግሮች እና የአፍ ውስጥ ንፅህና ባለመጠበቅ የሚመጣ መጥፎ የአፍ ጠረን ነው። ይህም የሚሆነው የአፍ እና የጥርስ ንፅህና በአግባቡ በማይጠበቅበት ጊዜ የምግብ ሽርፍራፊዎች በጥርስ እና በድድ መሃል እንዲሁም በጥርስ እና በጥርስ መካከል ሲከማቹ ጎጂ ባክቴሪያዎች ከምራቅ ጋር በመዋሀድ እነዚህን የምግብ ቅሪቶች እንዲሰባበሩ ስለሚያደርጉ ነው፡፡ ይህም ሂደት በሚከናወንበት ጊዜ የሚለቀቀው የሰልፈር ጋዝ መጥፎ የአፍ ጠረንን ያስከተላል፡፡

በመሆኑም ከሚከተሉት በአንዱም ሆነ በሌላው መንገድ የአፋችን ንፅህና ካልተጠበቀ መጥፎ የአፍ ጠረን ሊኖር ይችላል። እንደጥርሳችን ሁሉ ምላሳችንም ባግባቡ ፅዳቱ ካልተጠበቀ ብዙ ሸካራ እና ወጣ ገባ ያሉ ቦታዎች ስላሉት የምግብ ቅሪት እና ባክቴሪያዎች በቀላሉ አጠራቅሞ መጥፎ ጠረን ሊፈጥር ይችላል፡፡ አፋችን ውስጥ የተቦረቦረ ጥርስ ካለ በውስጡ ምግብ እና ባክቴሪያ ሊይዝ ስለሚችል ይህም መጥፎ ጠረን ሊያመጣ ይችላል፡፡ አፋችን ውስጥ የሰው ሰራሽ ጥርስ ካለና ይህ ጥርስ ባግባቡ ከድድ ጋር ካልገጠመ በመካከል ምግብ እና ባክቴሪያ ሊይዝ ስለሚችል የመጥፎ ጠረን መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ በድድ እና በጥርስ አቃፊ አካላት ላይ የጤንነት መጓደል ካለና የድድ መሸሽ፣ በጥርስ አቃፊ አካላት መካከል ክፍተት(periodontal pocket) ካለ ይህም ለምግብ እና ባክቴሪያ መከማቸት ዕድል ስለሚሰጥ መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያስከትል ይችላል፡፡

የአፍ መድረቅ ለአፋችን ንፅህና ምራቅ እራሱን የቻለ አስተዋፅኦ አለው። ይህም ማለት ምራቅ በበቂ መጠን አፋችን ውስጥ ካለ ያሉትን የባክቴሪያ እና የምግብ ቅሪቶች በማንሸራተት ወደ ውስጥ በመላክ ጠረን እንዳይፈጥሩ ይከላከላል፡፡ ምራቅ በተገቢው መንገድ ሳይመነጭ ቀርቶ አፍ ከደረቀ ግን ለባክቴሪያ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያመጣ ይችላል፡፡ የጉሮሮ፣ የእንጥል፣ የድድ፣ እንዲሁም የምላስ መቁሰል ወይም ኢንፌክሽን ካለ መጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤ ሊሆን ይችላል፡፡ ሲጋራ ማጨስና መጠኑ የበዛ አልኮል ማዘውተርም መጥፎ የአፍ ጠረን ሊያመጣ ይችላል። እንዲሁም በተፈጥሮ ከባድ ሽታ ያላቸው ምግቦች ለምሳሌ እንደ ቀይ እና ነጭ ሽንኩርት ያሉትን ምግቦች መጠቀም ጊዜያዊ የሆነ የአፍ ጠረን ለውጥ ሊያስከትል ይችላል። ምንም እንኳ እነዚህ ምግቦች የሚያመጡት መጥፎ ጠረን ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ በራሱ የሚጠፋ ቢሆንም፡፡

ሁለተኛው ከአፍ ውጪ ባሉ ችግሮች የሚመጣ የአፍ ጠረን ሲባል በውስጣዊ የሰውነታችን ክፍሎች ላይ በሚኖር በሽታ ምክንያት የሚከሰተውን የአፍ ጠረን ለውጥ ለማመላከት ነው፡፡ አንድ ሰው የኩላሊት፣ የስኳር፣ የጨጓራ ወይንም የጉበት በሽታ ካለበት ከበሽታው ጋር ተያይዞ የሚኖር የአፍ ጠረን ለውጥ ሊኖር ይችላል፡፡ አንዳንዴ የትንፋሽ ጠረን ለውጥ የውስጣዊ ችግሮች ጠቋሚ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ግን ማስተዋል ያለብን መጥፎ የአፍ ጠረን መንስኤ ውስጣዊ በሽታ ሊሆን ይችላል ሲባል ማንኛውም መጥፎ የአፍ ጠረን ያለበት ሰው ሁሉ ውስጣዊ ችግር አለበት ማለት እንዳልሆነ መረዳት ይገባል፡፡

መጥፎ የአፍ ጠረን መፍትሔ መጥፎ የአፍ ጠረን ሕክምና በትክክል መፍትሔ ሊያመጣ የሚችለው የጠረኑ መንስኤ በአግባቡ ተለይቶ ታውቆ ተገቢው ሕክምና እስከተደረገ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ከአፍ ውስጥ አካላት ጉድለቶች ጋር በተያያዘ የሚመጣ የአፍ ጠረን ትክክለኛው ሕክምና ከተደረገለት ሙሉ ለሙሉ የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው ተጠቂው ሐኪም ጋር ቀርቦ ጉድለት የደረሰበትን አካል ሲታከም ነው፡፡ ማለትም የተቦረቦረ ጥርስ ካለ በመሙላት፣ የተከማቸ ቆሻሻ ካለ በማንሳት፣ የአፍ ውስጥ ኢንፌክሽን ካለ በተገቢው መንገድ በማከም እንዲሁም ውስጣዊ የጤና እክልን በሕክምና በማስወገድ ይሆናል፡፡ የአፍ ውስጥ አካላት ችግሮች ተፈተው ጠረኑ ቀጣይነት ካለው ከውስጣዊ ችግሮች ጋር በተያያዘ ሊሆን ስለሚችል ውስጣዊ አካላት ላይ ምርመራ አካሂዶ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

በስተመጨረሻ የአፍ ጠረን ቢኖርም ባይኖርም ስለ ጥርስና አፍ ጤና አጠባበቅ ዘዴዎች በጤና ባለሙያዎች የተለያዩ ምክሮች ይሰጣሉ። ጠዋትና ማታ የጥርስ ሳሙና ተጠቅሞ በበቂ ሁኔታ ጥርስን ማፅዳት፣ የምንጠቀምበት ሳሙና የአገልግሎት ዘመኑ አለማለፉን ማጤን አስፈላጊ ነው። ሁሉንም የጥርስ ቦታዎች በለስላሳ ቡርሽ ከድድ ወደ ጥርስ መቦረሽ፣ ጥርስ ተጸድቶ ካለቀ በኋላ ምላስን ከኋላ ወደ ፊት በደንብ ማጽዳት፣ ከብሩሽ በተጨማሪ የጥርስ ማጽጃ ክር (dental floss) ተጠቅሞ ጥርስን ማፅዳት፤ በሐኪም የታዘዘ የአፍ መጉመጥመጫ ፈሳሽ ካለ በአግባቡ መጠቀም፤ ከስኳር ነፃ የሆኑ ማስቲካዎችን ማኘክ ይህም የምራቅ መመንጨትን ስለሚያበረታታ አፍን ጽዱ የማድረግ አቅም አለው። በተጨማሪም ምግብ ከተመገብን በኋላ አፍን በንጹህ ውሃ መጉመጥመጥ፣ ሲጋራ አጫሽ ከሆኑ ጭሱ የሚያመጣውን ውጫዊ የቀለም ለውጥ ሊያነሱ የሚችሉ ልዩ የጥርስ ሳሙናዎች ስላሉ እነርሱን መጠቀም ይገባል።

Read More

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here