Home Blog

‹‹የምንፈልገውን የፍትሕ ሥርዓት ለማምጣት አይቸግረንም ብዬ አምናለሁ›› ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት | The Reporter

0

ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው የፀደቀላቸው አዲሷ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ አዲሱ ቢሮአቸውን በመጎብኘት ሥራ ጀምረዋል፡፡ የሕዝብ አመኔታን ለመፍጠር ከሚሠሩ ሥራዎች መካከል አንዱ ፍርድ ቤቶችንና ቢሮአቸውን ለሕዝብ ምቹ ማድረግ ነው ሲሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሕዝብን የምናገለግልበት ተቋም የግድ ምቹ መሆን አለበት፤›› ብለው፣ ‹‹የምንፈልገውን የፍትሕ ሥርዓት ለማምጣት አይቸግረንም ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉም ተስፋቸውን አክለዋል፡፡

‹‹ከሁሉም በላይ ግን የሕግ የበላይነትን ማስከበር ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ እንደ ቀድሞው ጊዜ ፍትሕ የምናገኝበት ተቋም አለ ብሎ የሚያምንበት ደረጃ ለመድረስ የምንሠራቸው ብዙ ነገሮች አሉ፤›› ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

‹‹የፍትሕ ተቋማትን ወደምንፈልገው ደረጃ ለማድረስና መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች ሁሉ ለማስተካከል በመንግሥት በኩል ያለው ቁርጠኝነት ሥራችንን በነፃነት ለመሥራት የሚያስችለን መሆኑን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ስለዚህ ከፍትሕ አካላት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎችን በሙሉ ደረጃ በደረጃ እያስተካከልን እንሠራለን፡፡ በቅድሚያ መሠራት የሚገባቸውን ለይተን እንሠራለን፤›› ብለዋል፡፡

የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ስለሚኖር በዚህ መሠረት ሕዝብ አመኔታ የሚጥልበት ተቋም ለመፍጠር አይቸግርም ብለው፣ ‹‹ከሹመታችን በኋላ ከሕዝብ ያገኘነው ድጋፍ ደግሞ የምንፈልገውን ለማሳካት ትልቅ አቅም ይሆነናል፤› ብለዋል፡፡

‹‹ነፃ የፍትሕ ተቋም እንዲኖረን የሁሉም ፍላጎት ነው፡፡ ለውጥ ፈላጊው ሕዝብ በሙሉ ይህንን ይሻል፡፡ ነፃ የሆነ ፍርድ ቤት እንዳይኖር የሚፈልግ የለም፡፡ ስለዚህ የሕግ የበላይነትን ማስፈን አልተቻለም የሚለውን አመለካከት ሊቀይር የሚችል አሠራር ይኖረናል፡፡ በጥቅሉ ግን የምንፈልገውን የፍትሕ ሥርዓት ለማምጣት አይቸግረንም ብዬ አምናለሁ፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡

‹‹የሕግ የበላይነት ብዙ ጽንሰ ሐሳብ ያለበት ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ አንፃር ሕግን በጠበቀ መንገድ እንዲከናወን ማድረግ ነው፡፡ የሕግ የበላይነትን ለማስፈን ዳኞችን ብቻ ሳይሆን ጠበቆችንም ሕጉን ጠብቀው በአግባቡ መሥራትን የሚጠይቅ ስለሆነ፣ ሁሉም የበኩሉን በሕግ አግባብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ማድረግንም ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ያሉትን ሥራዎች በማከናወን ጭምር ነው አመኔታ ሊፈጠር የሚችለው፤›› ብለዋል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐሙስ ጥቅምት 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በሙሉ ድምፅ ሹመታቸው የፀደቀላቸው አዲሶቹ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊና ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ፣ ተቋሙን የሚጠበቅበት ኃላፊነት እንዲወጣ ከፍተኛ አደራና እምነት ተጥሎባቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ‹‹ተቋሙን ፍትሕ ፍትሕ የሚሸት ለማድረግ በተሿሚዎቹ እተማመናለሁ፤›› ማለታቸው በብዙዎች ዘንድ ድጋፍ ተችሮታል፡፡

ሁለቱም ተሿሚዎች የሕግ ባለሙያነታቸው በከፍተኛ የትምህርት ዝግጅትና በዳበረ ልምድ የተመሠከረለት በመሆኑም፣ የዳኝነት አካሉ በሕዝብ የተነፈገውን አመኔታ ለማስመለስ ይጠቅማል እየተባለ ነው፡፡ የዳኝነት አካሉን ነፃነትና ገለልተኝነት በተግባር በማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ተብለው የሚጠበቁት ተሿሚዎቹ፣ ለዚህ ታላቅ ኃላፊነት ከመመደባቸው በፊት ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመሠረተው 13 አካላት ያሉት የሕግና የፍትሕ ሥርዓት ማሻሻያ አማካሪ ምክር ቤት አባላት ሆነው መመደባቸው አይዘነጋም፡፡ አማካሪ ምክር ቤቱ የሚዲያ፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራትና የፀረ ሽብርተኝነት ሕጎችን ለማሻሻል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን ለማገዝ ነው የተመሠረተው፡፡

ወ/ሮ መዓዛ ከተሾሙ በኋላ በሰጡት አጭር መግለጫ፣ ‹‹ሕግ በተገቢው ሁኔታ በፍርድ ቤቶች ካልተተረጎመና ተገቢው ውሳኔ ካልተሰጠ ወረቀት ላይ ነው የሚቀረው፤›› ብለው፣ ‹‹የሕግ አምላክ ስንል የሕግ አምላክ ፍርድ ቤት ነው ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በማከልም በእርግጠኝነት መናገር የሚፈልጉት ሕዝብ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለው አመኔታ መመለስ እንዳለበት ነው፡፡ ይህም የመጀመሪያ ሥራቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ሕዝቡም ሕግ ለማስከበር ኃላፊነት አለበት ብለው፣ ‹‹መብታችንን የሚያስከብርልን ፍርድ ቤት ነው ብለን መጠበቅ የለብንም፤›› ብለዋል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ መብቱ እንዲከበርና ሕግ እንዲከበር የራሱንም የሌሎችንም መብት ማክበር ግዴታው እንደሆነ ማወቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ Read More

Ethiopia: በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በህገ ወጥ መንገድ ሊወጣ የነበረ ከ202 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ተያዘ

0

በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በህገ ወጥ መንገድ ሊወጣ የነበረ ከ202 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር እና ሌሎች በርከት ያሉ የገንዘብ ኖቶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴር የኮሙዩኒሚኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኤፍሬም መኮንን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ባለፉት 22 ቀናት በአውሮፕላን ማረፊያው በተደረገ ቁጥጥር 202 ሺህ 475 የአሜሪካን ዶላር በቁጥጥር ስር ውሏል።

ከዚህ በተጨማሪም 16 ሺህ 950 ዩሮ፣ 75 ሺህ 400 የአረብ ኢሚሬት ድርሃም፣ 2 ሺህ ፓውንድ፣ 6 ሺህ የስዊዝ ፍራንክ እና 34 ሺህ 800 የኢትዮጵያ ብር በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።

Sourec: FBC

BBC Ethiopia: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለኖቤል ታጭተዋል?

0

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡ በጥቂት ወራቶች ውስጥ ከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ማግኘት ብቻም ሳይሆን የኖቤል ሽልማት እንዲያገኙም ጭምር ዘመቻ እየተደረገላቸው ነው።

የኢትዮጵያ ዜጎችን ጨምሮ ከዚያም ባሻገር ዐብይ አሕመድ በአገር ውስጥና በአጎራባች አገሮች እያመጡ ያሉትን ጉልህ ለውጥ ተከትሎ ሽልማቱ ይገባቸዋል የሚሉ ድምጾች በርክተዋል።

በተለይም ከኤርትራ ጋር የጀመሩት የሰላም ጉዞ በደጋፊዎቻቸው የሽልማት “ይገባዎታልን” ዘመቻ ከፍ ብሎ ተሰምቷል።

እንደ ጎርጎሪዮሳዊያኑ አቆጣጠር በሐምሌ 23 የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ አማካሪ የነበሩት ኸርማን ኮኸን በትዊተር ገጻቸው ላይ የሚከተለውን ጻፉ- “በሞያ ዘመኔ ለመጀመርያ ጊዜ አንድ ሰው ለኖቤል እጩ ማድረጌ ነው፤ ያ ሰው ዐብይ አሕመድ ነው፤ ለአገሩ አሳታፊ ዲሞክራሲን ካመጣ መላው የአፍሪካ ቀንድ ወደተሻለ ቀጠና ይሸጋገራል።”

ይህ የኸርማን ጄ ኮኸን ሐሳብ ብዙዎች በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ ተጋርተውታል፣ አጋርተውታል።

ኖቤል በዘመቻ ይገኛል?
በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን እንደሚታየው ከሆነ ዶክተር ዐብይ ለእጩነት፣ አንዳንዴም ለአሸናፊነት ጫፍ ደርሰዋል። የሚያስፈልጋቸው የሕዝብ ድምጽ ነው የሚሉ መረጃዎች በስፋት ሲዘዋወሩ ሰንብተዋል።

ለመሆኑ የኖቤል የሽልማት ሥርዓት እንዲህ አይነቱን አሠራር ይከተላል? እነማን መጠቆም ይችላሉ?

ከኖቤል ሽልማት ይፋዊ ድረ-ገጽ እንደተገኘው መረጃ ከሆነ የኖቤል እጩዎች ጥቆማ የሚሰጠው በበቁ ሰዎች ብቻ ነው።

እነዚህ የበቁ ጠቋሚዎች የሚባሉት የሚከተሉት ናቸው።

• የአንድ ሉአላዊት አገር የካቢኔ አባላት ወይም የአገር መሪዎች

• የሄግ የግልግል ፍርድ ቤት ወይም የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት አባላት አልያም በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ወይም በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚገኙ ፕሮፌሰሮችና ተባባሪ ፕሮፌሰሮች

• ቀደም ብለው ኖቤል ያሸነፉ ሰዎች ወይም ያሸነፉ ድርጅቶች የቦርድ ሰብሳቢዎች

• የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የቀድሞም ሆኑ የአሁን አባላት

• የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ አማካሪዎች ናቸው።

ከላይ በተዘረዘሩት አባላት እጩው ሲቀርብ ነው ሕጉን ተከተለ የሚባለው። አንድ ሰው ራሱን እጩን አድርጎ ማቅረብ አይችልም።

የኖቤል ኮሚቴ አምስት አባላት ያሉት ሲሆን የኮሚቴው አባላት የሚሰየሙት በኖርዌይ ፓርላማ ነው።

ዐብይ አሕመድ ስለመጠቆማቸው ማን ሊነግረን ይችላል?
ኮሚቴው የእጩዎችንም ሆነ የጠቋሚዎችን ማንነት ለሚዲያም ሆነ ለእጩዎቹ በምንም መልኩ አይገልጽም። ማን ማንን ጠቁመ፣ እነማን እንዴት ተመረጡ ወይም ተጠቆሙ የሚሉ መረጃዎች የሚወጡት ሽልማቱ ከተካሄደ ከ50 ዓመታት በኋላ ብቻ ነው። ይህ ማለት ዐብይ አሕመድ የ2018 የኖቤል እጩ ስለመሆናቸው እርግጡን የምናውቀው በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2060 ይሆናል።

የኖቤል ኮሚቴው የጊዜ ሰሌዳ
መስከረም፡- በፈረንጆች መስከረም (ሴፕቴምበር) የኖርዌይ ኖቤል ኮሚቴ እጩዎችን ለመቀበል ይሰናዳል። እጩ የመቀበሉ ሥራ ለቀጣይ ስድስት ወራት ይጸናል። እጮዎቹን መጠቆም የሚችሉት ከላይ የተዘረዘሩት ብቁ ጠቋሚ የተባሉ ድርጅቶችና ግለሰቦች ብቻ ናቸው።

የካቲት፡- በየካቲት የእጩዎች መቀበያ ጊዜ ያበቃል። ከየካቲት 1 በፊት ያልተጠቆመ በዚያ ዓመት እጩ መሆን አይችልም።

መጋቢት፡-ኮሚቴው የእጮዎችን ዝርዝር ያቀርባል። ከእጮዎቹ ውስጥ ከ20 እስከ 30 የሚሆኑትን ብቻ ለተጨማሪ ማጣሪያ ይቀርባሉ።

ጥቅምት፦ በጥቅምት መጀመርያ ኮሚቴው አሸናፊውን በድምጽ ብልጫ ይመርጣል። ይግባኝ የማይባልበት ምርጫ ነው ታዲያ።

በታኀሳስ፦ 10 (በፈረንጆቹ) በኦስሎ ኖርዌይ የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ይካሄዳል።

የጊዜ ሰሌዳውና ዐብይ አሕመድ
የኖቤል ሽልማት ከአንድ ዓመት ዘለግ ያለ ጊዜን የሚወስድ ሂደት ነው። ኾኖም ጥቆማ የመቀበያ ጊዜ ከፈረንጆች መስከረም ጀምሮ ለ6 ወራት የሚዘልቅ ነው። ይህ እንግዲህ መጪውን የመስከረም ወር ሳይሆን የ2017ቱን ወር አንድ ብሎ የሚጀምር ነው።

የእጩ መስኮቱ ከተዘጋ ከሁለት ወራት በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት ዐብይ አሕመድ ቢያንስ የ2018 የኖቤል ሽልማት እጩ የመሆናቸው ነገርን አጠያያቂ ያደርገዋል። ምናልባት የኖቤል ኮሚቴው በመጨረሻዎቹ ጊዜያት እጩ የመጨመር ሥልጣን ስላለው ያ ተግባራዊ ከሆነ ጠባብ እጩ የመሆን እድል ሊኖራቸው ይችላል።

አልያ ግን ከወር በኋላ ጀምሮ ለ6 ወራት በሚጸናው የ2019 የኖቤል ሽልማት ለመካተት ካልሆነ በስተቀር፤ ዐብይ አሕመድ ከዚህ ውጭ በማንኛው አካል የሚደረገው ዘመቻ በኮሚቴው ምርጫ ሂደት ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ እንደማያደርግ ይታወቃል።

ተጨማሪ መረጃዎች
ይህ በእንዲህ እያለ በታሪክ ከፍተኛው የእጩ ቁጥር የቀረበው በ2016 ነበር። በዚያ ጊዜ የተመዝጋቢ እጩዎች ቁጥር 376 ሲሆን የዘንድሮውም ቀላል የሚባል አይደለም። 330 እጩዎች ቀርበዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዐብይ አሕመድ ይገኙበታል ወይ ነው ጥያቄው።

ዘንድሮ ከቀረቡት ከነዚህ እጩዎች ውስጥ 216 የሚሆኑት ግለሰቦች፣ 114ቱ ደግሞ ድርጅቶች ናቸው።

ይህ ሽልማት በ1901 ጀምሮ ለ96ኛ ጊዜ ተሰጥቷል።

ይህንንም ሽልማት 86 ግለሰቦች ወንዶች 16 ሴቶች እና 23 ድርጅቶች አሽንፈዋል።

የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ጉዳይ | Reporter

0

ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ ያጋጠመው ከፍተኛ አመፅና የፖለቲካ አለመረጋጋት የሰዎችን ሕይወት ከመቅጠፍና ንብረት ከማውደም ባለፈ፣ በኢኮኖሚው ላይ ያደረሰው ጉዳት ባይለካም እጅግ ከፍተኛ እንደነበረ መገመት አይከብድም፡፡ በተለይ በየዓመቱ እየተዳከመ የመጣው የወጪ ንግድ ግኝት ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ከፍተኛ መቀዛቀዝ ማሳየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ከሬሚታንስም (ሐዋላ) ሆነ ከወጪ ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ እጅግ ተዳክሟል፡፡ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ በገጠመው ችግር ሳቢያ ሕይወት አድን መድኃኒቶች ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት እስከማይቻልበት ደረጃ ደርሶ ከፍተኛ መሰናክል ፈጥሯል፡፡

የወጪ ንግድን በማበረታታት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ያሳድጋል በሚል እሳቤም መንግሥት የብርን የመግዛት አቅም በ15 በመቶ እንዲዳከም ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና ይህ አከራካሪ መፍትሕ እምብዛም ለውጥ አምጥቷል ለማለት የሚያስደፍር ክስተት እንደሌለ የሚከራከሩ ጥቂት አይደሉም፡፡

በአገሪቱ የተንሰራፋውን አመፅና ብጥብጥ ተከትሎም ዳያስፖራው ወገናችን እየተገደለ ወደ ኢትዮጵያ ገንዘብ አንልክም የሚል ዘመቻ በማድረግና መንግሥትን ለማዳከም በማለም፣ በቀጥተኛ መንገድ ገንዘብ እንዳይላክ ሲቀሰቅስ ቆይቷል፡፡ በዚህም ምክንያት በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል ከዚህ ቀደም ታይቶ የማያውቅ ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ሊፈጠር ችሏል፡፡

ይሁንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተሰየሙ በኋላ በወሰዷቸው የውጭ ምንዛሪ ማግኛ ዕርምጃዎች፣ የውጭ ምንዛሪ በእጃቸው የሚገኙ ሰዎች ገንዘባቸውን ወደ ባንክ እንዲወስዱ የሰጡትን ማሳሰቢያ ተከትሎ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቱ በመጠኑም ቢሆን መሻሻል አሳይቷል፡፡ በባንክና በጥቁር ገበያ መካከል የነበረው የሰፋ ልዩነት ሣንቲም ቤት ድረስ ወረዶ ነበር፡፡ ይሁንና ይህ ብዙም ሳይቆይ በጥቁር ገበያ ለውጥ መታየት ጀምሯል፡፡

የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ችግር ያገናዘበና ፈጠራ የታከለበት የተባለለት የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ እንዲቋቋም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት ጥሪና በወሰዱት ተነሳሽነት፣ ፈንዱን የማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ዳያስፖራው ለትረስት ፈንዱ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ በገንዘብ እንዲደግፍ ‹‹የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ›› በሚባል ስያሜ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከፍቶ ገንዘብ እየተጠራቀመ ይገኛል፡፡

የዚህ ትረስት ፈንድ ጠንሳሽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ዳያስፖራው በአገሩ የሚኖረው ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዲያድግ በተደጋጋሚ ጥሪ ሲያቀርቡ የነበረ ሲሆን፣ በተለይ ዳያስፖራው ለአገሩ ከማኪያቶ ላይ አንድ ዶላር በቀን ቀንሶ እንዲሰጥ የሚል ሐሳብ ለመጀመርያ ጊዜ የተነሳው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን በያዙ በሁለተኛው ሳምንት ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር በውጭ በተለይም በዱባይና በቻይና ገንዘባቸውን ያጠራቀሙ ሰዎች ዶላራቸውን እንዲያመጡ አሳስበው፣ ‹‹ኮንትሮባንድ ሌላው ወሳኝ ችግር ነው፡፡ ኮንትሮባንድ ማለት የዕቃ ብቻ አይደለም፡፡ የዶላር ኮንትሮባንድ አለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደምረው ነው የውጭ ምንዛሪ የሚባለው እንጂ፣ እናንተ እንደምትሉት የብሔራዊ ባንክ መመርያ ብቻ አይደለም፤›› ሲሉም የዶላር ግኝት ችግር ምንጭን አስረድተዋል፡፡

በወቅቱ ባደረጉት ንግግርም ዳያስፖራው መንግሥትን በሠልፍና በጽሑፍ እንዲቆነጥጥና በሬሚታንስ እንዳይጎዳ በማለት ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

ይኼንን ሐሳብ ይበልጥ ለመግፋት ከዳያስፖራው ጋር በቀጥታ ተገናኝተው ለመወያየት ከሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ቀናት በአሜሪካ ሦስት ከተሞች ጉብኝት አድርገው ነበር፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሎስ አንጀለስና ሚኒሶታ መድረኮች የተዘጋጁ ሲሆን፣ በመድረኮቹ ጎልተው ከተነሱ ነጥቦች አንዲ ይህ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ነው፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩና በሥፍራው መገኘት የቻሉ የአውሮፓና የካናዳ ነዋሪዎች የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በነበረው መድረክ ላይ የተገኘውና አጭር ንግግር ያደረገው ታማኝ በየነ፣ አንድ ዶላር ቢጠየቅም ሌሎችንም በማስተባበር አሥር ዶላር በቀን በማሰባሰብ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ቃል ገብቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበድር ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር የፈንዱን ጠቀሜት በእጅጉ ያጎሉ ሲሆን፣ ‹‹በቀን አንድ ዶላር ለምኛችኋለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ዓይነ ሥውራን እስካሁን ማስተማር የቻልነው አራት ፐርሰንት ብቻ ነው፡፡ ለእኔ አትርዱኝ፡፡ ረዳት ያጡ ዓይነ ሥውራንን አስተምሩ፤›› ብለዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ መሠረት በርካታ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን አስተዋፅኦ ለማድረግ ከፍተኛ ተነሳሽነት በማሳየታቸውም፣ በንግድ ባንክ በተከፈተውና የሒሳብ ቁጥሩም 1000255726725 በሆነ የፈንዱ ማጠራቀሚያ ገንዘብ ማጠራቀም ተጀምሯል፡፡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአካውንት ዳይሬክቶሬት የተገኘ መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በባንኩ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ዋና ኢኮኖሚስት አቶ በቃሉ ዘለቀ በተፈረመ ደብዳቤ አካውንቱ መከፈቱ ታውቋል፡፡ አካውንቱም በውጭ ምንዛሪ ገንዘብ የሚጠራቀምበት ሲሆን፣ ለጊዜው ገንዘቡ የማይንቀሳቀስ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይሁንና ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ በሚሰጠው ውክልና መሠረት ፈንዱን የሚያቀሳቅሰውን አካል ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲያስታውቅ፣ ፈንዱ የሚንቀሳቀስ እንደሆነም ታውቋል፡፡

በዚህ የሒሳብ ቁጥር ገንዘብ ማጠራቀም የሚፈልጉ የዳያስፖራው አባላት ከባንኩ ጋር በትብብር ከሚሠሩ 762 በላይ ባንኮች በተሳሰሩበት የባንኩ የስዊፍት አድራሻ “CBETETAA”፣ አልያም ከባንኩ ጋር በውል የሚሠሩ 20 የሐዋላ አስተላላፊ ድርጅቶችን በመጠቀም ገንዘብ ማጠራቀም እንደሚችም ተነግሯል፡፡

‹‹የእኛ ሚና ሒሳብ መክፈትና ገቢ የሚሰበሰብበትን መንገድ ማመቻቸት ብቻ ነው፣›› ሲሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ በልሁ ታከለ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የዚህ የዳያስፖራ ፈንድ መቋቋሙን የሚቃወሙ ባይኖሩም፣ አስተዳደራዊ የሆኑ ጥያቄዎች መልስ ሳያገኙና ሕጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም ሳይመሠረት ገንዘብ መሰብሰብ መጀመሩን የሚያጠይቁ በርካታ ባለሙያዎችና የዳያስፖራው አባላት አሉ፡፡

የሕግ ባለሙያ የሆኑትና በተለይ በሲቪል ማኅበረሰብ ሕግ ላይ ትኩረት የሚደርጉት አቶ ቁምላቸው ዳኜ እንደሚሉት፣ ይኼንን ዓይነት ተቋም ለመመሥረት የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በአገሪቱ እስካሁን የለም፡፡ ‹‹ነገር ግን የአደራ በጎ አድራጎት ድርጅት›› ማቋቋምን የሚደግፍ ድንጋጌ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት አዋጅ ላይ እንዳለ ይጠቅሳሉ፡፡ ይሁንና ትረስት ፈንዱ በዚህኛው የሕግ ድንጋጌ ሊሸፈን የሚችል እንዳልሆነም ያስረዳሉ፡፡

‹‹የዚህኛው ባህርይ ይለያል፣ እንደ ሕዝባዊ መዋጮ ዓይነት ባህርይም ይታይበታል፤›› ሲሉም ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህም የዳያስፖራ አካውንቱ ተከፍቶ ገንዘብ መጠራቀሙ የሕግ ማዕቀፉ ሳይበጅና ተቋማዊ ሳይደረግ መሆኑ አግባብነቱ ላይ እንደሚያጠያይቅም ይናገራሉ፡፡

‹‹ቀደም ብሎ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ቢሆን መልካም ነበር፡፡ አካውንቱ የተከፈተው በመንግሥት ነውና ያላግባብ ጥቅም ላይ የመዋል ዕድሉ ጠባብ ነው ሊባል ቢችልም፣ ሥርዓት ሊበጅለት ግን ይገባል፤›› ይላሉ፡፡

ነገር ግን የዳያስፖራ ፈንዱ የመንግሥት ተነሳሽነት ስላለበት፣ ካሁን በኋላም ሕግ ማውጣትና መተግበር እንደሚቻልም ያስረዳሉ፡፡

የትረስት ፈንዱ በቦርድ እንደሚመራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢናገሩም፣ አካውንቱ ተከፍቶ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ግን የተጓተተ የመሆኑን ምክንያታዊነት የሚጠይቁ አሉ፡፡

ነዋሪነታቸውን በለንደን ያደረጉት የፋይናንስ ባለሙያውና የፋይናንስ ዘርፍ ተንታኙ አቶ አብዱልመናን መሐመድ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መጠይቅ፣ ትረስት ፈንዱ መቼ ነው የተቋቋመው? አባላቱ እነማን ናቸው? በማንስ ተመረጡ? የቦርድ አባላቱ እነማን ናቸው? የሥራ አስፈጻሚዎቹስ? የውጭ ኦዲተርስ ተሹሞለታል ወይ? የመተዳደሪያ ደንቡንስ ከየት አግኝተን ማየት እንችላለን? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

በሌላ ወገን ደግሞ ለዚህ ትረስት ፈንድ ገንዘብ የሚያዋጡት ግለሰቦች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካላቸው ፍቅር እንጂ፣ በጉዳዩ አምነው ስላልሆነ ቀጣይነት ላይኖረው ይችላል የሚሉም አሉ፡፡ ስለዚህ ለዳያስፖራ ፈንዱ ግልጽነትና ተጠያቂነት የታከለበት አሠራር እስካልተዋቀረ ድረስ ሊቋቋም አይገባውም በማለት ይከራከራሉ፡፡ ለዚህም ከመንግሥት ዋስትና ይሻሉ፡፡

በትረስት ፈንዱ አካውንት ገንዘብ ያስገቡ ማርቆስ ፈለቀ (ዶ/ር) የሚባሉ ሐኪም በትዊተር ገጻቸው ላይ እ.ኤ.አ. የ2018 ግዴታቸውን 365 ዶላር ማስገባታቸውን ይፋ ሲያደርጉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍፁም አረጋ በትዊተር ገጻቸው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በርካታ አጋሮች የትረስት ፈንዱ አካውንት ይፋ ከተደረገ ጊዜ አንስቶ በደስታ ምላሻቸውን ሲያሳዩ ተስተውሏል፡፡ በድጋሚ ማሳወቅ የምንፈልገው ነፃ በሆነ፣ በግልጽነትና አጋሮቻችንን በማያስቀይም መንገድ ጥቅም ላይ እንደሚውል ነው፡፡ ይኼንንም በሚመለከት ተከታታይ ማብራሪያ እንሰጣለን፤›› ብለዋል፡፡

ዳያስፖራው በአገሩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ብቁ መረጃ እንደሌለው በመግለጽ፣ የተሻለ ቅርበት ያላቸው አካላት የማሳወቅ ግዴታቸውንም እንዲወጡ ጥሪ የሚያቀርቡ አሉ፡፡ የተሻለ እውቀት እንዲኖርም የትረስት ፈንዱ ማቋቋሚያ የሕግ ማዕቀፎች ሲዘጋጁ ለትችት እንዲረዱ ይፋ መሆን እንዳለባቸውም ይጠይቃሉ፡፡

የሲነርጎስ አማካሪዎች ቀጣናዊ ዳይሬክተር አቶ አበራ ቶላ የትረስት ፈንዱ መቋቋም በአገሪቱ ፖሊሲና በተግባር መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሚያግዝ ነው ይላሉ፡፡

‹‹መንግሥት ሀብት ያልመደበባቸው ሥፍራዎች በተለይም የፖሊሲ አካል ያልሆኑትና ብዙ ርቀት መጓዝ የሚጠይቁ የአካል ጉዳተኝነት ጉዳዮች ምላሽ እንዲያገኙ ያግዛል፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹የተዘነጉ ናቸውና እነዚህን አካል ጉዳተኞች ከቴክኖሎጂ ጋር ለማዋሀድም ይረዳል፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

እንደ አቶ አበራ ምልከታ፣ ዋናው ጉዳይ በትኩረት እየታቀደና ዲዛይን እየተደረገ ነው ወይ የሚሄደው የሚለው መታየት አለበት፡፡ ‹‹አንድ ጊዜ የመጣ ገንዘብ በርካታ ሥራ ሊሠራ ስለሚችል የዘላቂነት ጥያቄ ግን አይኖርበትም፤›› ብለዋል፡፡

ከዳያስፖራ ፈንዱ ጋር በተገናኘ ጥያቄ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በውጭ አገሮች የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራዎችን ለማከናወን፣ የሕግና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ማጤን ነው፡፡

ይህም በተለይ ሥጋት የሆነባቸው ግለሰቦች የሚጠቅሱት፣ ኢትዮጵያ ለህዳሴ ግድቡ ቦንድ በአሜሪካ በመሸጧ መቀጣቷን በማስታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመሸጫ ፈቃድ ሳታገኝ የሸጠችው ቦንድ ተመላሽ እንዲደረግና የስድስት ሚሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲጣልባት ተደርጎ ነበር፡፡

‹‹ትረስት ፈንዱን ለማቋቋም የሚወጣው ሕግ ይኼንን ጉዳይ በግልጽ ማስቀመጥ ይጠበቅበታል፡፡ በውጭ አገሮች እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶችን ሪፖርት የማድረግ ግዴታና ገደብ ስለሚኖር መጤን አለበት፡፡ ፈንድ መቋቋሙን በተመለከተ ሪፖርት ማድረግ ሊያስፈልግም ይችላል፤›› ሲሉ የሕግ ባለሙያው አቶ ቁምላቸው ያሳስባሉ፡፡

ካሁን ቀደም በኢትዮጵያ የዳያስፖራ ፈንድ ባይሆንም፣ የተለያዩ የትረስት ፈንዶችን የማቋቋም እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ተጠቃሽ የሆነው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንን ለማቋቋም ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ የሚገኘው የቅርስ መንከባከቢያ ትረስት ፈንድ ነው፡፡

ይህ ፈንድ በተቋሙ የቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ መምርያ ኃላፊነት እየተጠና የሚገኘው ትረስት ፈንድ ኮሚቴ ተዋቅሮ፣ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ፈንድ የማሰባሰብ ተሞክሮዎችን በመቀመር የሕግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት እየሠራ እንደሚገኝ፣ የመምርያው ኃላፊ አቶ ኃይሉ ዘለቀ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የዚህ ትረስት ፈንድ ማቋቋሚያ አዋጅ በ2011 በጀት ዓመት የመጀመርያው ሩብ ዓመት ተጠናቅቆ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በተለያዩ የሚመለከታቸው አካላት ከተገመገመ በኋላ፣ ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተልኮ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ይሁንታን አግኝቶ በፓርላማ አዋጁ እንደሚፀድቅ አቶ ኃይሉ ተናግረዋል፡፡

በአገሪቱ የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ጨምሮ ሌሎች ትረስት ፈንዶችን የማቋቋም እንቅስቃሴዎች ስላሉ፣ በተለይ ልምዶችን ከአፍሪካ በመቀመር ሕጉን እንዲያዘጋጅ ኮሚቴ መዋቀሩንም አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡

የዳያስፖራ ትረስት ፈንድን በተመለከተ የዳያስፖራው መነቃቃት ሳይቀዛቀዝ፣ በፍጥነት ወደ ተግባር መገባት እንዳለበት አቶ አበራ ያሳስባሉ፡፡ Reporter

አዲሱ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አህመድ አብዲ ማን ናቸው? BBC Amharic

0

የቀድሞውን የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሞሐመድ ኦማርን የተኩት አህመድ አብዲ ሼክ ሞሃመድ (ኤልካስ) በፊቅ ዞን ገርቦ በተባለ ስፍራ ተወለዱ ።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ በጊዜው በልማት ወደኋላ ለቀሩ ታዳጊ ክልሎች አገልጋሎት እንዲሰጥ በተቋቋመው ዕድገት አዳሪ ትምህርት ቤት ተምረዋል።

በ2001 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ፤ ወደ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በ2004 ዓ.ም በቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ትምህርት በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል።

ከምረቃ በኋላ በሶማሌ ክልል ጎዴ እና ጂግጂጋ ከተሞች የገቢዎች መስሪያ ቤት ባልደረባ ሆነው በመስራት የሥራ ዓለምን ተቀላቅለዋል ።

በ2006 ዓ.ም የቀብሪ ደሃር ከተማ ከንቲባ ሆነው የተሾሙ ሲሆን በቀጣይ ዓመት ደግሞ የክልሉ ምክትል የፋይናንስ ሃላፊ ሆነው ለመስራት ችለዋል።

ከ2008 ዓም ጀምሮ የክልሉ የፋይናንስ ቢሮ ዋና ሃላፊነትን ተረክበው የሰሩ ሲሆን ከሦስት ወራት ወዲህ የክልሉ የውሃ እና ፍሳሽ አገልግሎት ሃላፊ ሆነው እየሰሩ ነበር። በ2009 ዓ.ም ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በ’ዲዛስተር ማኔጂመንት’ ተመርቀዋል። በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ የሚገኙት አቶ አህመድ ሼክ ሞሐመድ ባለትዳር እና የሰባት ልጆች አባት ናቸው።

BBC Amharic

የጂግጂጋን ግጭት ሸሽተው የተሸሸጉ ሰዎች በከፋ ችግር ላይ ነን አሉ |BBC Amharic

0

በጂግጂጋ ሁከት ተቀስቅሶ ነዋሪዎች ሰላማቸውን ካጡ አምስት ቀናት አልፈዋል። ግጭቱን በመሸሽ በተለያዩ ስፍራዎች ተጠልለው የሚገኙ ዜጎችም ይሁን ከመኖሪያ ቤታቸው የማይወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች የውሃ እና የምግብ እጥረት እንደገጠማቸው ይናገራሉ።

ቅዳሜ ዕለት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ያልሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ለደህንነታቸው በመስጋት በአብያተ-ክርስቲያናትና በመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።

ዛሬ (ረቡዕ) በስልክ የነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ የሃገር መከላከያ ወደ ከተማዋ ከገባ በኋላ አንጻራዊ መረጋጋት ቢታይም የምግብ እና የመጠጥ ውሃ እጥረት ግን ለከፋ ችግር እየዳረጋቸው እንደሆነ ነግረውናል።

ለደህንነቱ ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው የከተማዋ ነዋሪ ”ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ ተጠልዬ ነው የምገኘው። አሁንም ለደህንነቴ ስለምሰጋ ወደ መኖሪያ ቤቴ መመለስ አልፈልግም። እዚህ ግን ከፍተኛ ችግር እየገጠመን ነው። በዕርዳታ የተሰጠንን ብስኩት ነው እየተመገብን ያለነው። ውሃ ግን አላገኘንም” ብሏል።

ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ደግሞ ”እስካሁን መንገድ ዝግ ስለሆነ ወደ ከተማዋ የሚገባ ምንም አይነት ነገር የለም። ቤት ውስጥ ያለንን ዱቄት በመጠቀም ቂጣ እየጋገርን ነው እየበላን የምንገኘው፤ እሱም እያለቀብን ነው። ከቀናት በኋላ ምን እንደምንሆን አናውቅም” ስትል ነዋሪዎች የገጠማቸውን የምግብ እጥረት ትናገራለች።

ከከተማዋ ነዋሪዎች መረዳት እንደቻልነው ከትናንት ማክሰኞ ጀምሮ የቧንቧ ውሃ ተበክሏል የሚል መረጃ በስፋት በመናፈሱ የከተማዋ ነዋሪዎች የመስመር ውሃ ከመጠቀም በመቆጠባቸው የውሃ እጥረቱን ከፍ አድርጎታል።

የክልሉ ተወላጅ የሆነ አንድ ግለለሰብ እንደሚለው ከሆነ ”በመጀመሪያ ደረጃ በጂግጂጋ ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት ነው ያለው። አሁን ደግሞ ውሃው ተመርዟል ተብሎ ሰው በውሃ ጥም እየተሰቃየ ነው” ይላል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ጨምረው እንደነገሩን ከሆነ የጸጥታ አስከባሪዎችም ሆኑ የመንግሥት አካላት ሸሽተው የሚገኙ የከተማዋ ነዋሪዎች ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ከመጠየቅ ውጪ ምንም አይነት ድጋፍ እየደረጉልን አይደለም በማለት ቅሬታቸውን ነግረውናል።

ነዋሪዎቹ መንግሥተ አስቸኳይ የምግብ እና የመጠጥ ውሃ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል። BBC Amharic

በሶማሌ ክልል የደረሰው ሰብዓዊና ፖለቲካዊ ቀውስ |Reporter

0

በሶማሌ ክልል ሕዝቦችና ነዋሪዎች ላይ የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰትና በክልሉ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ችግሮችን ለመፍታት ሐምሌ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በድሬዳዋ የተጀመረውን ጉባዔ ተከትሎ በጅግጅጋ የተቀሰቀሰው ግጭት የበርካታ ሰዎችን ሕይወት በማጥፋት፣ ንብረት በማውደምና ከፍተኛ ሥጋት በክልሉ ከፈጠረ በኋላ ወደ አንፃራዊ መረጋጋት ተመልሷል፡፡ እንዲህም ሆኖ በአካባቢው የሚኖሩ ወገኖች ምግብና ውኃ በፅኑ ከመቸገራቸውም በላይ፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉም በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ማለዳ በሶማሌ ክልል በጅግጅጋ ከተማ የተቀሰቀሰው ግጭት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊት በክልሉ እንዲሰማራ ከተደረገ በኋላና የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ ዓብዲ ዑመር መሐመድ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኗል፡፡ በክልሉ ለሁለት ቀናት የቆየው ግጭት እንዴት ሊቀሰቀስ ቻለ?

የሶማሌ ክልል የአገር ሽማግሌዎች፣ የቀድሞ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ምሁራን፣ የተለያዩ ምክር ቤቶች አባላትና በውጭ የሚኖሩ የሶማሌ ተወላጆች በክልሉ የሚስተዋሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ፖለቲካዊ ችግሮች ላይ ለመምከር፣ ሐምሌ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በድሬዳዋ ከተማ ቀጠሮ ይዘዋል፡፡ ያቀዱትን ጉባዔ ለማካሄድም ከከተማዋ አስተዳደር አስፈላጊውን ፈቃድ ቀድመው ካገኙት በኋላ፣ ስብሰባው በሰላም እንዲጠናቀቅ ጥበቃ እንዲደረግላቸው አመልክተው ይሁንታን አግኝተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ጉባዔ መካሄድ የለበትም ብሎ ያወጀው የሶማሌ ክልል አስተዳደር የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ለጉባዔው ፈቃድ መስጠት እንደሌለበት በይፋ ከመጠየቅ አንስቶ ከፍተኛ ጫና ሲያደርግ መቆየቱን፣ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኢብራሂም ኡስማን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹በከተማ አስተዳደሩ ላይ የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ፈጥሮ የነበረው ጫና ቀላል አልነበረም፡፡ ነገር ግን ስብሰባው እንዳይካሄድ ለመከላከል በቂ ምክንያት አልነበረንም፡፡ አንደኛ ይህ የዜጎች መብት እንጂ የምንፈቅደውና የምንከላከለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ሁለተኛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ አይደለንም፤›› ሲሉ ከንቲባው አስረድተዋል፡፡

ጉባዔውን ያዘጋጁት አካላት የጠየቁትም ጥበቃ እንዲደረግላቸው እንጂ የተለየ ፈቃድ አለመሆኑን የተናገሩት ከንቲባ ኢብራሂም፣ ተሰብሳቢዎቹ የጠየቁት ጥበቃ በሚያርፉበት ሆቴልና በመሰብሰቢያ አዳራሹ እንዲመደብ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከሶማሌ ክልል የተሰነዘረው ምላሽ እጅግ አስገራሚና ሥርዓተ አልበኝነት የታየበት ነበር ብለዋል፡፡

‹‹ስምንት መኪና የታጠቀ ኃይል የድሬዳዋ ከተማ ከሶማሌ ክልል በምትዋሰንበት በሽንሌ ዞን በኩል መጣ፡፡ ነገር ግን በሥፍራው የፌዴራል የፀጥታ ኃይል ስለነበር ከድንበር አላለፈም፡፡ በዚህ በኩል ሳይሆን ሲቀር ተልዕኮ የተሰጣቸው ወጣቶች ወደ ከተማዋ እንዲዘልቁና ስብሰባው እንዲጨናገፍ እንዲያደርጉ ተሰማርተው ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ወጣቶቹ ገንዘብ በመርጨት ስብሰባው እንዲደናቀፍ ጥረት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ የከተማዋና የፌዴራል ፀጥታ አካላት ተቀናጅተው ስብሰባው በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ ማድረግ ችለዋል ብለዋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ የተካሄደው ጉባዔ በሶማሌ ክልል ላለፉት አራት ዓመታት የተስተዋሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የፖለቲካ መብቶች መጨፍለቅና የግለሰብ የበላይነት የነገሠበት ሥርዓተ አልበኝነት፣ እንዲሁም መደረግ በሚገባቸው መፍትሔዎች ላይ በመወያየት የፌዴራል መንግሥትና ክልሉን የሚመራው የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ) በጋራ ተንቀሳቅሰው ሕጋዊ የፖለቲካ ሥርዓት በክልሉ እንዲያሰፍኑ ጫና መፍጠር መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ የሚታየው አጠቃላይ የፖለቲካዊ ሥርዓት መንቀጥቀጥ መነሻ ምንጩ በሶማሌ ክልል የሰፈነው የአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነትና በግለሰቡ ዙሪያ የተሰበሰቡ የጥቅም ተጋሪዎች ጭፍን እንቅስቃሴ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡

ይኼንን ችግር በፍጥነት መቅጨት ካልተቻለም ኢትዮጵያን የማፍረስ አደጋ የማስከተል አቅም እንዳለው ያስረዳሉ፡፡

የሶማሌ ክልልን መገንጠልና የጅግጅጋ ቀውስ

በድሬዳዋ ከተማ ሐሙስ ሐምሌ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. የተጀመረውን ስብሰባ ማደናቀፍ ያልቻለው በጅግጅጋ ከተማ የከተመው የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ካቢኔ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ሊያፈርስ የሚችል ድብቅ ሴራ ነድፎ ቅዳሜ ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ውሳኔ የማሳለፍ ዕቅድ መያዙን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን ገልጸዋል፡፡

ይህ ዓላማም በጥቂት የክልሉ ካቢኔ አባላት ጠንሳሽነት የክልሉን ምክር ቤት አባላት በኃይል በማስገደድ፣ የሶማሌ ክልል ከኢትዮጵያ እንዲገነጠል ውሳኔ ማሳለፍ እንደነበር ባለሥልጣኑ ያስረዳሉ፡፡

በጉዳዩ ላይ መረጃ የደረሰው የፌዴራል መንግሥት እንቅስቃሴው የጥቂት የከሰሩ ፖለቲከኞች ሴራና ኃይልን ተጠቅሞ በማስገደድ ሊፈጸም የታቀደ መሆኑን በመገንዘብ፣ በጅግጅጋ ከተማ የሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ማንቀሳቀሱን ተናግረዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ የተንቀሳቀሰው የክልሉ ምክር ቤት አባላትን በማስገደድ ሊፈጸም የነበረውን ፀረ ዴሞክራሲያዊና ሕግን ያልተከተለ እንቅስቃሴ ከማስቆም የዘለለ ዓላማ እንዳልነበረው እኚሁ ከፍተኛ ባለሥልጣን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የታቀደው ሴራ የተደረሰበት መሆኑን የተረዳው የጀግጅጋው ውስን የካቢኔ ስብስብ፣ የከተማውን ሰላም የማደፍረስ ተግባር ውስጥ መግባቱን ለዚህም የተደራጁ ወጣቶችንና የክልሉን ፖሊስ ማንቀሳቀሱን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የተነሳ በጀግጅጋ የሚኖሩ የሌላ ብሔር አባላትን በመለየት ማጥቃት፣ መዝረፍና የእምነት ተቋማትን ማቃጠል ቅዳሜና እሑድ በመፈጸም በሺዎች የሚቆጠሩ የጅግጅጋ ነዋሪዎች ሸሽተው በቤተ ክርስቲያናት እንዲጠለሉ መገደዳቸውን የተገኙት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማቲያስ ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን በሰጡት መግለጫም፣ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን ይፋ በማድረግ ድርጊቱን አውግዘዋል፡፡ በሌላ በኩል የተቃጠሉት አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር ከዚህም በላይ መሆኑ ተሰምቷል፡፡

በሁለት ቀናት በተሰነዘረው ጥቃት ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ የነዋሪዎችን ንብረት የመዝረፍና የማውደም፣ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማትንም እንዲሁ በግልጽ የመዝረፍ ተግባር መፈጸሙ ታውቋል፡፡ በጅግጅጋ ከተማ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት እንዲወድም ተደርጓል፡፡ ይህ ሁሉ ሲፈጠር የፌዴራል የፀጥታ ተቋማት ወደ አካባቢው በመዝለቅ የመከላከል ተግባር አለመፈጸማቸው ጥያቄ አስነስቷል፡፡

ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን መግለጫ የሰጡት የፌዴራል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ፣ ከሰኞ ከቀትር በኋላ አንስቶ የመከላከያ ሠራዊት እንዲሰማራ መታዘዙን ተናግረዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊቱ የተሰማራውም የክልሉ መንግሥት በጅግጅጋና አካባቢው የተከሰተውን ቀውስ ለመቆጣጠር ከአቅም በላይ በመሆኑ፣ የፌዴራል የፀጥታ አካላትን ድጋፍ በመጠየቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ሥልጣኔን ከምለቅ ብሞት እመርጣለሁ››

በዋናነት በጀግጅጋ ከተማና በሌሎች የሶማሌ ክልል ከተሞች ከቅዳሜ ጀምሮ የተከሰተው ቀውስ በክልሉ መንግሥት ጥቂት አመራሮች እነሱ ያደረጁት ቡድንና የፀጥታ ኃይሉ የፈጠረው መሆኑን ሚኒስትሩ አቶ አህመድ አስረድተዋል፡፡

ምክንያቱን ሲያብራሩም የሶማሌ ክልል ተወላጆች በድሬዳዋ ከተማ ያካሄዱት ስብሰባ የሶማሌ ክልል አመራሮች ከሥልጣን እንዲለቁ የታቀደ እንደሆነ በመገመት፣ ‹‹ሥልጣን ልቀቅ ተብያለሁ በማለት የክልሉ አመራር›› የቀሰቀሰው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ተግባር ውስጥም የክልሉ ልዩ ኃይል ፖሊስ ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ በግጭቱ እንዲሳተፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ አመራሮች በሙሉ ሳይመክሩበትና ስለጉዳዩ አስፈላጊነት እንኳን ሳይገነዘቡ፣ የሶማሌ ክልልን የመገንጠል እንቅስቃሴ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ ‹‹ሥልጣኔን ከምለቅ ሞት እመርጣለሁ›› በማለት በቀውስ ውስጥ የመሸሸግና አገርን የማፍረስ አደጋ ያዘለ እንቅስቃሴ መሆኑን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

የተፈጠረውን ቀውስ በተመለከተ የኢሶሕዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ እድሪስ ኢብራሂም በተደጋጋሚ መረጃ እንዲሰጡ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም፡፡ ይሁን እንጂ ለቢቢሲ ሶማሊኛ ፕሮግራም ቅዳሜ ቀን በሰጡት አስተያየት ክልሉን የመገንጠል እንቅስቃሴ መኖሩን አስተባብለዋል፡፡

‹‹ለጊዜው ለመገንጠል አላሰብንም፣ በፌዴራል ሥርዓቱ እንተዳደራለን፡፡ ነገር ግን መገንጠል ምንም ሐሳብ አይደለም፣ ሕገ መንግሥቱም ለዚህ ዋስትና ይሰጣል፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን የመከላከያ ሠራዊቱ ቅዳሜ ዕለት በሕገወጥና ከሕገ መንግሥቱ በተቃራኒ፣ የሶማሌ ክልል ምንም ዓይነት ጥያቄ ሳያቀርብለት በጅግጅጋ ከተማ መሰማራቱን ኃላፊው አውግዘዋል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከሥልጣን መልቀቅ

የፌዴራል መንግሥት ክልሉን ከሚመራው ኢሶሕዴፓ አመራሮች ጋር የተፈጠረውን ቀውስ መፍታት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሲመክር ቆይቶ፣ ሰኞ ዕለት ከውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡

በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሠረት የመከላከያ ሠራዊቱ በክልሉ የፀጥታ ማስከበር ተግባር ለመፈጸም፣ የዚያኑ ዕለት በፍጥነት በጅግጅጋ ከተማ መሰማራቱን መንግሥት ይፋ አድርጓል፡፡

ሌላው ጉዳይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ አሌ) ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ስምምነት ከተደረሰ በኋላ፣ የሥልጣን መልቀቂያ እንዲያቀርቡና በፓርቲው ሕገ ደንብ መሠረት የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር በጊዜያዊነት ርዕሰ መስተዳድሩን ተክተው እንዲሠሩ መወሰኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ከፍተኛ ባለሥልጣን ገልጸዋል፡፡

ይህ ውሳኔ ተደፈጻሚ የሆነው በክልሉ ፓርቲ በኩል በመሆኑ፣ የሕጋዊነት ቅደም ተከተሉ በቀጣዮቹ ጊዜያት በክልሉ ምክር ቤት እንደሚፈጸም ምንጮች አስረድተዋል፡፡

ይኼንንም የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ እድሪስ ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ተቋማትን የማጠናከርና የሕግ ተጠያቂነትን ያረጋግጣል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በጅግጅጋ ከተማ አንፃራዊ ሰላም ቢሰፍንም፣ ነዋሪዎች አሁንም ፍራቻ እንዳላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስ ሰላም ማስፈን መጀመራቸው ግን ተስፋ እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል አሁንም የምግብና የተለያዩ አቅርቦቶች ችግር እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ ከጅግጅጋ ከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች ግን አሁንም ችግር መኖሩን አስረድተዋል፡፡

የአገር መከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ለኢቲቪ ማክሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት በስልክ እንደገለጹት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል ፖሊስ በማረጋጋት ላይ ናቸው፡፡ በሌሎች የክልል ከተሞች መከላከያ በማረጋጋት ላይ መሆኑንና ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡ Reporter

የኦሕዴድን ስያሜና ዓርማ ለመተካት ሐሳብ ቀረበ |Reporter

0

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ከ28 ዓመታት በላይ እየተጠራበት የሚገኘውን ስያሜውን፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በሚል ስያሜ ለመተካትና ዓርማውን ለመቀየር ሐሳብ ቀረበ፡፡

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ማክሰኞ ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው፣ ኦሕዴድ የሚለውን የድርጅቱን ስያሜ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ በሚል ስያሜ በመተካት፣ የፖለቲካ መሠረቱ የሆኑት የኦሮሚያ አርሶ አደሮችና የከተማ ነዋሪዎችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማሳተፍና ለማገልገል መታሰቡን ይፋ አድርጓል፡፡

ከመጠሪያው በተጨማሪም የሚገለገልበትን ዓርማ ለመለወጥ ሦስት ዓርማዎች ለውሳኔ ያቀረበ መሆኑን፣ የፓርቲ ሰንደቅ ዓላማ (ባንዲራ) የማያስፈልግ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሚገለገልበት ዓርማና መጠሪያ የፖለቲካ ተልዕኮን የማያመለክት፣ በግለሰብ ደረጃም ለተለያዩ የንግድ ተግባራት ለሚቋቋሙ መገልገያ በመሆኑ ይኼንን መጠሪያ ለመቀየር አንደኛው ምክንያቱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ድርጅት የሚለውን ስያሜ ለመተካት የተለመዱት አማራጭ የፖለቲካ ፓርቲ ስያሜዎች ማለትም ንቅናቄ፣ ትግልና ግንባር የሚሉት መጠሪያዎች ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ተግባራትን ከመግለጽ ይልቅ ውስን የሆነ የፖለቲካ ተግባርንና የትጥቅ ትግልን የሚያመላክቱ በመሆናቸው ፓርቲ የሚለውን መጠሪያ መታሰቡ ተገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሚገለገልበትን ዓርማም ለመቀየር ሦስት አማራጭ ዓርማዎች የቀረቡ ሲሆን፣ የአባ ገዳ ሥርዓት መገለጫ የሆኑትን ጥቁር፣ ቀይና ነጭ ቀለማት ከኦዳ ምልክት ጋር በተለያዩ ሦስት አቀማመጦች ለውሳኔ አቅርቧል፡፡

የኦሕዴድ ድርጅታዊ ጉባዔ በተያዘው ወር ውስጥ የሚካሄድ ስለሆነ፣ የቀረቡት ዓርማዎችና መጠሪያ ስያሜ ላይ ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ላይ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡

የስያሜ ለውጡ ለኦሮሞ ሕዝብ የሚታገሉ ሌሎች ፓርቲዎችን በአንድ ጥላ ሥር ለማምጣት የሚያስችል ቅድመ እንቅስቃሴ መኖሩን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦሕዴድ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

ኦሕዴድ ለኦሮሞ ሕዝብ ለዓመታት ሲታገሉ የነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በጋራ የመሥራት ዕቅድ እንዳለው፣ ከተወሰኑት ጋርም የመጀመርያ ውይይት ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በተለያዩ አገሮች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የኦሮሞ ሕዝብን የሚወክሉ ፓርቲዎች በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅሰቃሴ ለመሳተፍ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ሕጋዊ ዕውቅና ለማግኘት የምዝገባ ጥያቄ አለማቅረባቸውን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ Reporter

በኢትዮጵያ ድሮንን ለህክምና አገልግሎት ለማዋል የቴክኖሎጂ መረጣ እየተካሄደ ነው| EBC

0

በኢትዮጵያ ድሮንን ለህክምና አገልግሎት ለማዋል የሚያስችል የቴክኖሎጂ መረጣ እያካሄደ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የድሮን ቴክኖሎጂን በመጠቀም ምንም አይነት የትራንስፖርት አገልግሎት በማያገኙና ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ ገጠራማ አካባቢዎች እስከ 5 ኪሎ ግራም የሚደርስ እንደ ክትባት፣ ደም እና ሌሎች መሰረታዊ የነብስ አድን መድሀኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶችን ለማድረስ ያስቻላል፡፡

እንደ ጎርፍና ግጭት ባሉ ምክንያቶች የመንገድ መዘጋት ቢያጋጥም የነብስ አድን መድሀኒቶችና ደም በአስቸኳይ ለማድረስ እንደሚጠቅምም በጤና ጥበቃ ሚንስቴር የጤና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዳይይሬክተር አቶ እዮብ ከበደ ለኢቢሲ ገልፀዋል፡፡

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በ2 ሳምንታንት ጊዜ ውስጥ የድሮን ቴክኖሎጂ መረጣውን አጠናቆ በቀጣይ አመት አገልግሎቱን ለማስጀመር ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡ EBC

የጤና ጥበቃ ሚስቴር ከሲቪል አቪዬሽን፣ ከመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን ስለትግበራው ምክክር እንዳደረገም አቶ እዮብ ገልፀዋል፡፡

ጤና ጥበቃ ሚንስቴር የጤና አገልግሎትን ለማፋጠን የድሮን ቴክኖሎጂን ሩዋንዳ በመሄድ በስራ ላይ ከሚገኘው የዚፕ ላይን የድሮን ቴክኖሎጂን አሰራር ያጠና ሲሆን ከዚሁ በአገራችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር የድሮን ቴክኖሎጂ ፕሮጀክት በመጠቀም አገልግሎቱን መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመስራት ላይ መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታወቋል፡፡ EBC

 

በአዲስ አበባ የተበላሹና ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉ ምግብ ነክ ምርቶች ተያዙ |EBC

0

በአዲስ አበባ 71 ሺ ኪሎ ግራም የተበላሹ እና ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉ ምግብ ነክ ምርቶች፣ 53 ሺ ሊትር የተበላሹ የለስላሳ ምርቶች እንዲሁም ከ2ሺ600 በላይ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው መድሀኒቶችን በቁጥጥር ስር በማዋል ማስወገዱን የአዲስ አበባ ምግብ መድሀኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደር እና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።

የጤና አገልግሎት ጥራትና ብቃትን ለማረጋገጥ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ መቻሉን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አለምፀሀይ ጳውሎስ ተናግረዋል።

ባለስልጣኑ የሚያደርገውን ክትትል እና ቁጥጥር በሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ ህብረተሰቡ እና የሚመለከታቸው አካላት ግንዛቤ በመፍጠር በኩል የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

መንግስት በህገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ላይ የሚወስደው ዕርምጃ ጠንካራ እና አስተማሪ ሊሆን ይገባል ተብሏል።EBC